
ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መጋቢት30//1998 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 129/1998 ዓ.ም አማራ ቤቶች ልማት በሚል በኘሮጀክት ጽ/ቤትነት ደረጃ ተቋቁሞ ለአምሰት ተከታታይ ዓመታት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲያከናውን የነበረ፤ግንቦት 4/2003 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 83/2003 ዓ.ም ከጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የመንግስት ግንባታዎችን በተቋራጭነት እንዲገነባና በአማካሪነት ደግሞ የቁጥጥር ስራዎችን እንዲሰራ ወደ ኤጀንሲ ደረጃ ያደገ፤ መጋቢት 25/2007 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 131/2007 ዓ.ም ደግሞ ደረጃ አንድ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ (BC-1) ሆኖ በደንብ ቁጥር 177/2010 ዓ.ም አማራ ሕንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በብር 964,838,269.00 ካፒታል ይዞ በማቋቋም 1 የሕንፃ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ፣ 2 የግንባታ ግብዓት ማምረቻ ማዕከላት፣ 4 የጠጠር ማምረቻ ማዕከላት፣ 2 የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ጥራት ፍተሻ ማዕከላት፣ 188 ማሽነሪዎች፣ 146 ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም 1,231 ሰራተኞችን በመያዝ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ለአብክመ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 136/2008 ዓ.ም በሰጠው ስልጣን መሰረት ቀደም ሲል አማራ ሕንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በሚል ተቋቁሞ ሲንቀሳቀስ የነበረን የልማት ድርጅት ለመስተዳድር ም/ቤት አቅርቦ በማጸደቅ በደንብ ቁጥር 215/2016 ዓ.ም በአዲስ መልክ ለተሸለ ተልዕኮና ኃላፊነት ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በሚል የስምና የአደረጃጀት ለውጥን አድርጓል፡፡
ዘመን በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የገባያ ክፍተት ለመሙላት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት ከግንባታና ተዛማጅ ስራዎች ያገኘውን ትርፍ ለክልላችን ህዝብ ቋሚ ሀብት በሚፈጥሩ ጉዳዮች እና በሌሎች ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በተለያዩ ድርጅቶች አክሲዮኖችን በመግዛት ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጨማሪ በዋና የንግድ ባለድርሻነት ሰባት የንግድ ተቋማትን በብር 438,645,256 በመስራችነት ያቋቋመ ትልቅ አሴት ያለው ተቋም ነው፡፡ ለኮርፖሬሽናችን የቢዝነስ አድማስ ማስፋፋት ስትራቴጅክ ጉዳይ ሲሆን በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚካሄዱ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በመሳተፍ የኮርፖሬሽኑን ኢኮኖሚካል ጥቅም ከማስገኘት ባሻገር በክልሉ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ እና ማህበረሰቡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡
ዘመን አሁን ላይ በአክሲዎን ድርሻው ከፍ ያለ ሲሆን ለአብነት ያህል የአባይ ባንክ አ.ማ፣ አባይ ኢንሹራንስ አ.ማ፣ ጎሽሜዳ ፓይፕና ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አ.ማ፣ አመልድ G+25 3መንትያ ሕንጻ አዲስ አበባ ለገሀር ላይ ያለ ኮምሌክስ ሕንጻ እና ሰቆጣ ሴራሚክስ አ.ማ ላይ ግንባር ቀደም መስራች የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት ነው፡፡
ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ነገር የራሱ የሆነ ሀብት እንዲኖረው የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ ሲሆን አሁን ላይ ባህርዳር በሚገኘው በዋናው ቢሮ መስሪያ ቤቱ ለቢሮና ለንግድ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘ ባለ3 መንትያ B+G+7+0G+5 ሕንጻዎችን ገንብቶ አገልግሎት እያገኘ ያለ ሲሆን በደሴ ከተማ ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች ለቢሮና ለንግድ የሚውል B+3+G+9 የሆነ ዘመናዊ ሕንጻ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው 884 የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች፣ 32 የቢሮና የንግድ ተቋማት ፣88 ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ፣5 የሚሆኑ የባህል ማዕከላት 24 የዩኒቨርስቲ ሕንጻዎች 31 የኢንዱስትሪ መንደር እና ሸዶች ፣ 95.8 ኪ.ሜ የጠጠርና አስፓልት መንገዶች በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች እንዲሁም ከክልሉ ውጭ በቢኒሸንጉል ጉምዝ ክልል ማህበራዊ የትምህርት ተቋማትን በጥራት ገንብቶ ለደንበኞች አስረክቧል፡፡
ዘመን በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልላችን ባሉ ከተሞች ከ15.4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ከ 29 በላይ የህንጻና ከ3 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከG+0 እስከ G+17 የቢሮና የንግድ ቤቶችን ህንጻዎችን ፣ ትልልቅ ሆስፒታሎችን፣ ዘመናዊ ቄራ፣የባህል ማዕከላትን፣ሎጅዎችን፣የኢንዱስትሪ ሕንጻዎችን፣የጠጠርና የአስፓልት መንገዶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን እያሳደገ ያለ ተቋም ሲሆን አሁን ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችንና አሰራሮችን በማዘመን ወደ ተግባር ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ ሲሆን የኮርፖሬሽኑን አሰራር ለማዘመን የERP እና BIM ሶፍት ዌሮችን ወደ ተግባር በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ መዋቅርም አስጠንቶ በቦርድ ያስጸደቀ ሲሆን አሁን ላይ ስራው የቀሩትን ውሱን ተግባራት አሟልቶ የተሻለ አደረጃጀትና አወቃቀር ወይም የአሰራር ለውጥ ለማምጣት በሂደት ላይ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ የፕሮጀክት ሰራተኞችን ጨምሮ ወንድ 2474 ሴት 787 ድምር 3261 ቋሚ ሰራተኞችና ወንድ 2167 ሴ 330 ድምር 2497 ኮንተራት ሰራተኞችን ይዞ በመስራት ላይ ነው፡፡ በማሽንና ተሸከርካሪ ሀብቱ ደግሞ 936 ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ያሉት ግዙፍ አቅም ያለው ተቋም ነው፡፡
ዘመን ከሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ማህበራዊ ሀላፊነትን ከመወጣት አኳያ በክልሉ ከሚገኙ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኝ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን በየጊዜው አቅመ ደካሞችን በመርዳት ፣ ወላጅ አልባ ለሆኑ ህጻናት የትምህርት ቤት ቁሳቁስ በማሟላት፣ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ በክልሉ ካሉ አረንጓዴ ልማቶች በችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመሳተፍ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡